Reading Articles

Current Articles | Categories | Search | Syndication

Sunday, October 28, 2007
የኢትዮጵያ ሚሌኔዬም
By mnegusse @ 11:42 AM :: 905 Views :: 2 Comments :: :: General
 

ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ ግዚአብሔር

“ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትረጋለች!”                            

እንኳን ለሚሌኔዬም አደረሳችሁ!

በፓ/ር ኤፍሬም ላእከማርያም 

አገራችን ኢትዮጵያ ከሦስት ሺ ዓመት በላይ ታሪክ ያስቆጠረች ፥ ነጻነትዋም በእግዚአብሔር ኃይልና ጸጋ ተጠብቆ የቆየች፥ በመጽሐፍ ቅዱስም ከ 40 ጊዜ በላይ ስሟ የተጠቀሰ አገር ነች።
ከክርስቶስ ልደት በፊት በአገሪቱ ዉስጥ ከቆዩት ነባር እምነቶች ሌላ ከደቡብ አረብ በፈለሱ ሳባዉያን አማካይነት የተቋቋመ በጸሐይና ጨረቃ ምልክትነት የሚመለክ አምልኮ እንደነበር   በየሐ፥ በአክሱም፥ በአዶሊስና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ፍርስራሽ ቅርሶች፥ የገንዘብ አንቲካዎችና የድንጋይ ጽሑፎች ይመሰክራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ሕገ-ኦሪትን ተቀብላ እዉነተኛዉን የአብርሃም አምላክ (ያህዌ) ስታመልክ መቆየትዋ በታሪክ የሚታወቅ ከመሆኑም በላይ በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በተለይ በጣናና አካባቢዋ የሚገኙ የጥንት ሴማዊ መሰዊያዎች ይመሰክራሉ፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አባቱ ካረገ በኋላ በ35-37 ዓ/ም አካባቢ ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዘዉ ኢትዮጵያዊ ባለስልጣን የሕገ-ኦሪት አማኝ እንደነበረ አዲስ ኪዳን ይጠቁማል (የሐዋ.ሥ. 8፥26-38)፡፡ ስለዚህም ባለሥልጣን “የኢትዮጵያ ንግስት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ...ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር ... ሲመለስም በሰረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበርይላል፡፡
እንደ ሕገ-ኦሪትም ኢየሩሳሌም ተገኝቶ ስግደቱንና የሃይማኖት ግዴታዉን ተወጥቶ ነገር ግን ስለ ነፍሱ በቀራንዮ መስቀል የሞተለትን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል የምስራች ሳይሰማ ይመለስ ስለነበር ይህንን አይቶ እግዚአብሔር ራራለትና መንፈስ ቅዱስ ወንጌላዊ ፊልጶስን ከሰማርያ (ዌስት-ባንክ) ወደ ጋዛ ልኮለት ተገናኙ፡፡ ፊልጶስም ከሚያነበዉ የኢሳይያስ መጽሐፍ (ምዕ. 53) ተነስቶ ስለ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ሰማያት ወርዶ፥ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፥ ስለ በደላችንና ኃጢአታችን በቀራንዮ መስቀል ተሰቅሎ፥ ሞታችንን ሞቶ ነገር ግን ሞትን ድል ነስቶ እንደተነሳ፥ በዚሁም ከአዳም ከወረስነዉ ጥንተ-አበሳና ኩነኔ በደሙ እንደዋጀንና ይህም እግዚአብሔር ራሱ “በደሙም የሆነ ማስተሰሪያ አድረጎ”  እንዳቆመዉ “በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ እንደ ተገለጠ፥ እርሱም ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንደሚገኝ (ሮሜ 3) ወንጌል ሰበከለት፡፡
በዚህ መልክ የወንጌል ብርሃን ከበራለት በኋላ ወዲያዉ “እነሆ ዉኃ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድነዉ?” ብሎ ጠየቀ፡፡ መልሱም በእየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለዉ እምነት እንደሆነ ተነገረዉ፡፡ ወዲያዉም “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ “ በማለት “ በልቡ አምኖ በአፉም መስክሮ (ሮሜ 10፥10) ደህንነትን (Salvation) ስለተቀበለ ተጠምቆ ወደ እናት አገሩ በደስታ ተመለሰ፡፡ ለዚሁም የቤተክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ ቅዱስ አዉሳብዮስ “ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” ተብሎ የተጻፈዉ ትንቢታዊ ቃል በዚህ ግዜ ተፈጸመ በማለት አስምሮበታል፡፡ ከዚህ በመነሳት ክርስትና ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የገባዉ በዚሁ ሰዉ እንደሆነ ይታመናል፡፡
ኋላም በ4ኛዉ ክፍለ-ዘመን በቅዱስ አትናትዮስ ዘእስክንድርያ እጅ የተሾሙት አቡነ ሰላማ (ፍሬምናጦስ) ከንጉሱ ከኢዛና ጀምሮ ለሕዝቡ ሁሉ ወንጌል ስለ ሰበኩ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ክርስትና የአገሪቱ እምነት ሆኖ በይፋ ታወጀ፡፡ ወንጌል ብርሃን ነዉ “በጨለማ የሄደ ህዝብ ብርሃን አየ” ይላልና፡፡ ወንጌል የእግዚአብሔር ኃይል ነዉ፤ ከሰይጣን እስራትና ከኩነኔ አርነት ያወጣልና፡፡ ወንጌል የእርቅና የሰላም መልዕክት ነዉ፤ “እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና”  እንዳለ ቅዱስ ጳዉሎስ (2ቆሮ. 5)፡፡ የሚገርመዉ ነገር ታራቂና አስታራቂ እግዚአብሔር ራሱ መሆኑ ነዉ፡፡ ስለሆነም ክርስትና ከሌሎች የሚለየዉ በዚህ ነዉ፡፡ ሌሎች በብዙ ጥረትና የጽድቅ ሥራ እግዚአብሔርን ለማግኘት ሰዎች ከምድር ወደ ሰማይ የሚያቆሟቸዉ መሰላሎች ሲሆኑ ክርስትና ግን እግዚአብሔር ራሱ ሰዉን ለማግኘት ወደ ምድር የወረደበት በክርስቶስ ከራሱ ያስታረቀበት የራሱ መለኮታዊ አሰራር ነዉ፡፡
ሩፊነስ የተባለ ታሪክ ጸሐፊ እንደሚተርክልን የፍሬምናጦስ ወንድም ኤዴስዮስ ወደ አገሩ ሶርያ ሄዶ እዚያዉ ቄስ ሆኖ ሲኖር በኢትዮጵያ የፈነጠቀዉ የወንጌል ብርሃን ያለ መሪ እንዳይቀርና እንዳይዳፈን ትልቅ ሸክም የተሰማቸዉ ፍሬምናጦስ ግን የቤተሰባቸዉንና የአገራቸዉን ናፍቆት ወደ ጎን ትተዉ ለወንጌል ሥራ ቅድሚያ በመስጠት ወደ አሌክሳንድርያ ሄደዉ እዚያ ለሚገኙ አባቶች ሪፖርት ሲያቀርቡ ቅዱስ አትናትዮስ “ከአንተ የተሻለ ማንን ልንልክ ነዉ?” በማለት እርሳቸዉን የመጀመሪያ ጳጳስ አድርጎ ሾማቸዉ፡፡ ይህንንም የሰላምና የዕርቅ ወንጌል የሰበኩትን እኚሁ አባት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን “አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን” በማለት በመዓረግና በክብር ሰየመቻቸዉ፡፡
ከሐዋርያት ሥራና ከቅዱስ አዉሳብዮስ ምስክርነት እንዲሁም በ4ኛዉ ክፍለ ዘመን ከምናየዉ ሰፊ ታሪክ አንጻር ከእስራኤል ቀጥሎ ወንጌልን ከተቀበሉት አገሮች ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ እንደሆነች በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡
ስለሆነም የኢትዮጵያ ሚሌኔም የዘመን መለወጫ ብቻ ሳይሆን ክርስትና ላለፉት 2000 ዓመታት ተጠብቆ እኛጋ መድረሱንም የምናከብርበት ቀን ነዉ፡፡ እንደገናም ዘመን በተጨመረ ቁጥር የጌታችን ዳግም ምጽአቱ ከመቸዉም ግዜ እየቀረበ ስለሆነ የምንዘጋጅበትም ጭምር ነዉ፡፡ መጨረሻዉ መቅረቡን የሚጠቁሙ ምልክቶች እየታዩ ነዉና (ማቴ. 24)፡፡ አዳኛችን በክብር ዳግመኛ ሲመጣም ኢትዮጵያዉያን ታላቅ የአምልኮና የስግደት ድርሻ እንደሚጠብቃቸዉ ቅዱስ መጽሐፍ ይናገራል፦
      “ከባሕር እስከ ባሕር
      ከወንዝም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይገዛል
      በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ
      ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ...” (መዝ 72፥8-11)
“ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚማልዱኝ የተበተኑት ሴቶች ልጆቼ ቁርባኔን ያመጡልኛል” (ሶፎ. 3፥10)
እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት ግን በዳግም ምጽአቱ ዕድል-ፈንታ የሚኖረን ከክርስቶስ ጋር በሚኖረን ግንኙነት መሰረት እንጂ በዜግነት ብቻ አይደለም፡፡ መጽሐፍ እንደሚያስተምረዉ በዚህ ዓለም ማንም ሰዉ የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ወራሽ የሚሆነዉ በክርስቶስ አየሱስ ሲያምን ብቻ ነዉ፡፡ለዚህም አይነተኛ ምሳሌ ከላይ የተጠቀሰዉ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ነዉ፡፡ ይህ ሰዉ ኢየሩሳሌም ድረስ ስግደት ሄዶአል፥ የነቢዩ መጽሐፍ በእጁ ነበር፥ ያነበዉም ነበር፡፡ ይህ ግን ሐይማኖታዊ ስራ እንጂ ነፍስን የሚያድን ስላልሆነ መንፈስ ቅዱስ ፊልጶስን ልኮ የክርስቶስን ወንጌል እንዲሰማና ለደህንነቱ በክርስቶስ እንዲያምን ዕድል ሲሰጠዉ እናያለን፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም የሚናገሩት ስለ ክርስቶስ ነዉ (ዮሐ. 5፥39)፡፡ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ የተፈጠሩትና የተጋጠሙት በእርሱ መሆኑን ነዉ (ዮሐ. 1፥3፤ ቆላ. 1፥16-17)፡፡ ሆኖም እኛን በመዉደዱ ምክንያት ክብሩን በገዛ ፈቃዱ ትቶ ወረደ፥ የባርያን መልክ ይዞ በሰዉም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ...ራሱን አዋረደ...ለሞትም ያዉም ለመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ (ፊል. 2)፤ ደዌአችንን ተቀበለ፥ ሕመማችንንም ተሸከመ፥ ስለ መተላለፋችን ቆሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ...በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን...(ኢሳ. 53)፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገዉ፥ ከስምም ሁሉ በላይ ስም ሰጠዉ፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነዉ (ፊል. 2)፡፡
ስለሆነም ቅዱስ ጴጥሮስ፦ “መዳንም በሌላ በማንም የለም፥ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና!” ሲል አስጠንቅቆአል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም፦ “እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደሰጠን፥ ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነዉ፡፡ ልጁ ያለዉ ሕይወት አለዉ፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለዉ ሕይወት የለዉም!” (ዮሐ. 5፥11-12) በማለት የዘላለም ሕይወት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ አበክሮ አስተምሮአልና የነፍስ ጉዳይ ስለሆነ አግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን፡፡
ልዑል እግዚአብሔር አገራችንን ኢትዮጵያን ይባርክልን!
የሕዝቧን አንድነትና ሰላም ይጠብቅልን!
ዓይነ-ልቡናችንን አብርቶ ከቅዱስ ቃሉ የሰማነዉን በልባችን ያሳድርልን!
አሜን  

 

 

Rating
Comments
By Semere @ Wednesday, October 31, 2007 10:08 AM
Timely teaching, pastor. Thanks....

By fake watches on sale @ Friday, November 25, 2011 1:42 AM
Another very popular way to save the most money while shopping online is to look into online auctions.

Click here to post a comment