Current Articles | Categories | Search | Syndication
የዳዊት ሕይወት (ጥናት #16) የዳዊት ጸሎት ለመንፈስ ቅዱስ ምሪት በፓ/ር ኤፍሬም ላእከማርያም "ቅዱስ መንፈስህም በጽድቅ መንገድ ይምራኝ!" መዝ. (143፡10) መግቢያ፦ ባለፈው ጥናታችን ላይ "ፈቃድህን ማድረግ አስተምረኝ" የሚለውን የዳዊት ጸሎት አይተናል። በዚሁ ክፍል ደግሞ የጸሎቱ ሁለተኛውን ክፍል እንመለከታለን። ዳዊት የጸለየው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ ብቻ ሳይሆን ለማድረግ ነው። እግዚአብሔር ፈቃዱን ለቅዱሳኑ ቢያንስ በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ይገጻል። 1ኛ. በቃሉ፣ 2ኛ. በመንፈሱና 3ኛ. በሁነታዎች። ቅዱስ ዳዊትን ብቻ ሳይሆን እኛንም በከበረው የልጁ ደም የተዋጀን ልጆቹ ስለሆንን ዛሬም በመንፈሱ ይመራናል (ሮሜ 8)። ስለሆነም ፈቃዱን ለማወቅ ብቻ ሳይሆን ለማድረግ ወይም ለመታዝዝ እንደ ዳዊት ልንጸልይ ይገባል፣፡ መታዘዝ የሌለበት እውቀት ብቻውን ከንቱ ነው (ያዕ. 1፣22-25)። Vincent Aslop (1703) የተባሉ የእግዚአብሔር ሰው "እውቀት ያለ መታዘዝ አንካሳ ነው፣ መታዘዝ ያለ እውቀትም እዉር ነው፣ እውርንና አንካሳን ካቀረብን ደግሞ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እናገኛለን ብለን ተስፋ ማድረግ ፈጽሞ የለብንም" ብሏል። የሁላችን ጥያቄም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ብናውቅም እንዴት መታዘዝ ይቻላል? ገና ያልተዋጀና የወደቀ ሥጋ የተሸከምን፣ በወደቀ ዓለምም የምንኖር ስለሆንን እንዴት በመታዘዝ ሕይወት መመላለስ እንችላለን? የሚል መሠረታዊ ጥያቄ ሊሆን ይችላል። ለዚሁ መልሱም በዚሁ ጥናታችን የምናተኵርበት "ቅዱስ መንፈስህ..." የሚለው ቃል ነው። አዎን በራሳችን ኃይል ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ! በእርግጥ የእብራይስጡ ቃል የሚለው «ሩዋሓ ጦብ» "መልካሙ መንፈስህ" ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን መልካምም ስለሆነ የመታዝዝ ሕይወት ይኖረን ዘንድ ኃይል ይሰጠናል፣ ያስተምረናል፣ ይመራናል። ስለሆነም ነህምያ "ያስተምራቸው ዘንድ መልካሙን መንፈስህን ሰጠሃቸው" (9፣20) ብሎ ይላል። ያለ መንፈስ ቅዱስ ሰው ከንቱ ነው፣ ጠማማ መንገድንም ይከተላል፤ ያለ መንፈስ ቅዱስ ምሪት ሕይወት፣ ኑሮ፣ አገልግሎት ሁሉ ድካም ብቻ ይሆናል። ዳዊት ራሱ በቍ. 4 ላይ "ነፍሴ በውስጤ አለቀችብኝ" ሲል እንመለከታለን። እኛም እንደዚሁ ሕይወታችንንና አካሄዳችንን ለመመርመር በዚሁ ጥናት ጌታ ይረዳን ዘንድ ጸሎቴ ነው፦ በዚሁ ድረ-ገጽ (ዌቭ-ሳይታችን) ያለውን "በመንፈስ ተመላለሱ" በሚል ርዕስ የተጻፈውን 'ዲቮሽናል' ከዚሁ ክፍል ጋር በተዛማጅነት ያንብቡና የሚቀጥሉትን ጥያቄዎች ይመልሱ። 1. ስለ መንፈስ ቅዱስ አስፈላጊነት ከዳዊት ጸሎት የተረዱትን ይግለጹ? 2. የመንፈስ ቅዱስ ምሪት ለግል፣ ለቤተ ሰብ፣ ለቤተ ክርስቲያን የሚኖረውን አስተዋጽኦ ከጸሎቱ የተረዱትን ይግለጹ? 3. በአንጻሩም ሊመራቸው የተሰጣቸው የእግዚአብሔር መንፈስ "ተመልሶ ጠላት ሆናቸው" የሚል ቃል በኢሳ. 63፣10-14 እናነባለን። ለምን? በአዲስ ኪዳን ዘመንስ እንዲህ ዓይነት ችግር ያለ ይመስልዎታል? 4. ከላይ ካለው ጥያቄ ቍ. 3 ብዙም ባልተለየ መንገድ (ዮሐ. 14፣25-26፤ 16፣8-15 ያሉትን ተጨማሪ ምንባቦች ያንብቡና) የእግዚአብሔር መንፈስ በክርስቲያን ሕይወት ስለሚኖረው ዋና ድርሻ የተረዱትን በማጠቃለል ይግለጹ። 5. እርስዎስ እንዲህ ዓይነት ጸሎት ከዚህ በፊት ጸልየው ያውቃሉ? አሁንስ?