Current Articles | Categories | Search | Syndication
በመንፈስ ተመላለሱ! (πνεύματι περιπατειτε) ገላ. 5፡16 በፓስተር ኤፍሬም ላእከማርያም በጥንታዊው የግሪክ ቋንቋ (Coine Greek) "ፔሪፓቴኦ" የሚለው ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ 95 ጊዜ ተጽፎ እናገኘዋለን። ትርጉሙም መሄድ፣ መመላለስ፣ መኖር፣ ራስን መግራት ማለት ሲሆን ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ 5፣16 ላይ "πνεύματι περιπατειτε ኒዩማቲ ፔሪፓተይተ" "በመንፈስ ተመላለሱ፣ በመንፈስ ኑሩ፣ በመንፈስ ሂዱ፣ በመንፈስ ራሳችሁን ምሩ" በሚል ቃል ለአማኞች ትልቅና መሠረታዊ ትምሕርት ያስተላልፋል፤ በኤፌሶን 5፡18 ላይም "መንፈስ ይሙላባችሁ..." ብሎ ይናገራል። ጌታን ከማወቃችን በፊት በበደላችንና በኃጢአታችን ምክንያት መንፈሳችን ሙት ነበር (ኤፌሶን 2፣1)። ጌታን ካገኘን በኋላ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ ውስጣችን ገብቶ አዲስ ሕይወትን ሰጠን፣ በመንፈስም ሕያዋን ሆንን (ሮሜ 8፣10-11)፤ ያን ጊዜ መንፈሳዊ ዓይናችን ተከፈተ፣ ያኔም ማን መሆናችን ብቻ ሳይሆን የማን መሆናችንን ተረዳን። ሰው ጌታን ባያውቅ ራሱን አያውቅም፣ ስለዚህም በ16ኛው ክፍለ-ዘመን ከነበሩት የተሐድሶ መሪዎች አንዱ ጆን ካልቪን (John Calvin) "ሰው በመጀመሪያ እግዚአብሔርን ካላወቀ ራሱን (ማንነቱን) በእርግጠኝነት ወደ ማወቅ ደረጃ ፈጽሞ አይደርስም" ብሏል። ታድያ በዘመናችን እግዚአብሔርን የማያውቁ ሰዎችና የEvolution ሊቃውንት ነን ባዮች በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረውንና ክቡር የሆነውን ሰው "እንስሳ ነው" ወይም "ከእንስሳት አንዱ ነው" ብለው ቢናገሩ ምን ያስደንቃል? እርግጥ ነው የሰው ልጅ በራሱ ጥረት እግዚአብሔርን ሊያውቅ አይችልም፣ እግዚአብሔርን ካላወቀ ደግሞ የራሱን ማንነትና ለምን ዓላማ እንደተፈጠረም ማወቅ ፈጽሞ አይችልም። ምክንያቱም ከውድቀት በኋላ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የኃጢአት ግድግዳ ስላለ (ኢሳ. 59፣1-8)፤ በዚህም ምክንያት ሰው ከእግዚአብሔር በመራቁ መንፈሳዊ ነገሩና አምላኩን የማወቅ ችሎታው ሁሉ የጨለመ ስለሆነ ነው። ጌታ ኢየሱስን እንደግል አዳኛችንና ጌታችን አድርገን ስንቀበል ግን በመንፈስ ተወልደን የእግዚአብሔር ልጆች እንሆናለን (ዮሐ. 1፣11-12፤ ሮሜ 8፣14-16)፣ ስማችንም በሕይወት መጽሐፍ ይጻፋል (ራዕ. 3፣5፤ 13፣8፤ ዕብ. 12፣23)፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ይኖራል፣ የነበረንንም ዓለማዊ ባሕርይ በየቀኑ እየቀረፈ የጌታን ባሕርይ ያለብሰናል፣ እየተለወጥንም እንሄዳለን። ይህም ማለት የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን ሥልጣን (መብት) ወዲያው ጌታን ስንቀበል (በዳግም ልደት) የምናገኘው እውነት ሲሆን የሕይወት ለውጥ ግን ቀስ በቀስ የሚያድግ እንጂ ቅጽበታዊ (Instantaneous) አይደለም፣ ይህም ከቃሉ ጋር ካለን ግኑኝነትና ከመታዘዝ ጋር ተዛማጅነት አለውና። ስለሆነም አማኝ ጌታን ካገኘበት ሰዓት ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ በሕይወቱ ይኖራል፤ መንፈስ ቅዱስ ዳግም ለተወለደው አዲሱ ሰውም ዕድገት ይሰጠዋል፣ ያጠነክረዋል፣ ያበረታዋልም። ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ "በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር እንደ ክብሩ ባለ ጠግነት መጠን ይስጣችሁ" (ኤፌ. 3፣14-16) ይላል።ስለሆነም ጌታን ካገኘን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት እንዲኖረንና በመንፈስ እንድንመላለስ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። መንፈስ ቅዱስ፡- 1. የተለወጠ ሕይወት እንዲኖረን ያደርጋል፣ ማለትም የአሮጌው ሰው ባሕርያችንን (ዝሙት፣ ርኵሰት፣ መዳራት...) ከሕይወታችን እያስወገደ በመንፈስ ፍሬ ይተካዋል። 2. ስለሆነም ኃጢአትን አሸንፈን በድል ሕይወት እንድንመላለስ ያደርገናል። 3. በውስጣችን የእግዚአብሔር ፍቅር ስለሚፈስ የፍቅር ሕይወት እንዲኖረን፣ በፍቅርም እንድንመላለስ ያደርገናል። 4. ለእግዚአብሔር የተሰጠ ሕይወት ማለትም የመታዘዝ ሕይወት እንዲኖረን ያደርገናል። 5. ግራ ከመጋባት ያወጣናል፣ ስንደክም ያበረታናል፣ ስናዝንም ያጽናናል። 6. ያስተምረናል፣ ወደ እውነት ሁሉ ይመራናል (ዮሐ. 14፣15, 26፤ 16፣12-15፤ 1ዮሐ. 2፣27፤ ሮሜ) ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ጌታን ከተከተሉ ብዙ ዓመታት ቢሆንም ከዓለም ብዙም የተለዩበት ነገር ላይኖር ይችላል፤ አልፎ አልፎም ይህንን...ያንን...መተው አቃተኝ፣ ከኃጢአት መላቀቅ አቃተኝ፣ ምን ባደርግ ይሻልኛል? የሚሉ ይኖራሉ። መልሱም ባጭሩ በመንፈስ መሞላት ወይም በመንፈስ መመላለስ ነው። ይህም ራስን ለጌታ ከመስጠት ጀምረን መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን እንዲሰራ መፍቀድ ይኖርብናል። በመንፈስ እንድንመላለስና በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት እንዲኖረን ደግሞ በቅድስናና በንጽሕና መኖር ያስፈልገናል። ከሰዎች ጋር አብረን ለመኖር ማንነታችውንና ባሕርያቸውን ጠንቅቀን ማወቅ እንደሚኖርብን ሁሉ እንደዚሁም አማኞች ከሆንን በሕይወታችን ውስጥ የሚኖረውን መንፈስ ቅዱስን ማንነቱንና ባሕርዩን ከቃሉ እየመረመርን በነጻነት ነገር ግን በጥንቃቄ ልንመላለስ ያስፈልገናል (ኤፌሶን 4፣30)። ለምሳሌ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ከቅድስና ከሚያጎድለን አካሄድ ሁሉ ማለትም በአነጋገር፣ በአመለካከት፣ በአጠቃላይ በመንፈሳዊ ሕይወታችን፣ በባሕርያችንና በአኗኗራችን ላይ መጥፎ ዝንባሌና ተጽእኖ ከሚያመጡብን ዓለማዊ ጓደኞች ፈጽመን መለየት ይኖርብናል። ከመጥፎ ጓደኞች ሕብረት እንዳይኖረን ወስነን ካልተለየን ግን ሕይወታችን ፈጽሞ ሊቀየር አይችልም። ውሳኔ ማድረግና መለየት ካልቻልን ደግሞ እጅ ተጭኖ ቢጸለይ፣ ከኮንፍራንስ - ኮንፍራንስ ብንካፈል፣ ከቤተ ክርስቲያን ወደ ቤተ ክርስቲያን ብንዞር፣ ብዙ ብንጮህና ብናለቅስ ለውጥ አይመጣም። እንዲያውም በአገራችን ምሳሌያዊ አነጋገር «ከአጋም ጋር የተጠጋች ቍልቋል እያለቀሰች ትኖራለች» እንደሚባለው፣ አማኞች እንደመሆናችን መጠን ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ በድል ሕይወት ልንመላለስ ሲገባን መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ካልከበረ ወይም አኗኗራችን እርሱ የሚያዝንበት ከሆነ የሚኖረን ሕይወት ለውጥ የሌለው ሃይማኖት ብቻ፣ ኑሮአችንም የለቅሶ ኑሮ ብቻ ይሆናል። እናስተውል! ከምንም ነገር ይልቅ በጌታ ያገኘነው አዲስ ሕይወት ይበልጥብናል። ቅዱስ ዳዊትም ይህን ስለሚያውቅ እንዲህ ብሎ ጸለየ፦ "ከፊትህ አትጣለኝ፣ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ የማዳንህን ደስታ ስጠኝ" መዝ. 50(51)፣11 ይህን ሲያነቡ ምን ተሰማዎት? የእርስዎስ ጸሎት ምን ይሆን? ለጌታ ያልተለዩበት፣ ከዓለም ጋርም የተመሳስሉበት፣ ለመንፈስ ቅዱስም ያልተመቹበት ክፍተት በኑሮዎና በአካሄድዎ ይኖር ይሆን? ለኃጢአትስ የተከፈተ ቀዳዳ በሕይወትዎ ይኖር ይሆን? በዚህ ጽሑፍ ከተጻፈው መልዕክት በተጨማሪ ጌታ "ራቅ" ፤ "ተለይ" ያለባቸውን ክፍሎችና ሁኔታዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ፈልገው በማንበብ ሕይወትዎን ይመርምሩ! ሕይወትዎ "እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው፣ ቅዱስም መሥዋዕት" አድርገው እንዲያቀርቡ እንጸልይልዎታለን (ሮሜ 12፣1)። የጸሎት እርዳታ ካስፈለግዎ ወይም ሊያገኙን ከፈለጉ በአድራሻችን ይደውሉልን ወይም ይጻፉልን! ጌታ ይባርክዎ!